Sorry, you need to enable JavaScript to visit this website.

ohr

Office of Human Rights
 

DC Agency Top Menu

የዲሲ የሰባዊ መብቶች ቢሮ(OHR) የኦክቶበር 2026 ወርሃዊ ጋዜጣ፣ የዳይሬክተሩ መልእክት (Amharic)

ውድ ነዋሪዎች፣ ጎረቤቶች እና ወዳጆች፦

ወደ 2027 የበጀት ዓመት ስንሸጋገር፣ የኦክቶበር ወር መብቶቻችንን የመረዳትና እርስ በርስ የመደጋገፍን አስፈላጊነት እንዲሁም ሁሉም ሰው በክብር፣ በእኩልነት እና በመከባበር የሚስተናገድባቸውን ማህበረሰቦች የመገንባትን ጉዳይ ለማሰብ እድል ይሰጠናል። በዚህ ወር፣ የጉልበተኝነት መከላከል ወርን፣ የLGBTQIA+ ታሪክ ወርን፣ የአካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት ግንዛቤ ወርን እና በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም ጥቃትን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን እናከብራለን። እያንዳንዱ የመታሰቢያ ክንውን፣ የሰብአዊ መብቶችን ማስከበር መድልዎ ሲያጋጥም ምላሽ ከመስጠት ያለፈ ነገር እንደሚጠይቅ ያስታውሰናል። ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች ለራሳቸውና ለሌሎች ለመሟገት የሚያስፈልጋቸውን እውቀት፣ ግብዓትና ድጋፍ ማቅረብ ማለት ነው።

በዚህ ወር ከተለየ ትርጉም ካላቸው ክንውኖች አንዱ ከወጣት የሰብአዊ መብት አምባሳደሮቻችን ጋር መገናኘታችን ነው። ስለሚወዱትና ስለሚጓጉለት ነገር የመስማት፣ ለጥያቄዎቻቸው መልስ የመስጠት እንዲሁም ይህንን ሥራ እንድሠራ ያነሳሳኝን ነገር የማካፈል እድል አግኝቼ ነበር። ለሰብአዊ መብቶች ያላቸው ከፍተኛ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት፤ ደህንነታቸው የተጠበቀና ሁሉንም ያካተቱ ማህበረሰቦችን በመገንባት ረገድ ወጣቶች ወሳኝ አጋሮች መሆናቸውን ያስታውሰኛል። በወጣቶች ጉልበተኝነት መከላከያ ፕሮግራማችን አማካኝነት፣ ተማሪዎችን፣ ቤተሰቦችን እና አስተማሪዎችን በግጭት አስተዳደር፣ በሳይበር ጉልበተኝነት፣ LGBTQIA+ ወጣቶችን በመደገፍ እና ጉልበተኝነትን መቼ እና እንዴት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው በመለየት ተግባራዊ ግብዓቶችን እናቀርባለን።

ተጋላጭ የሆኑ ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ የምናደርገው ጥረት አረጋውያንን ጭምር ያካትታል። የLGBTQIA+ ታሪክ ወርን ምክንያት በማድረግ፣ በረጅም ጊዜ እንክብካቤ መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚኖሩ የLGBTQIA+ አረጋውያንን እና ከኤችአይቪ (HIV) ጋር የሚኖሩ አረጋውያንን መብቶች ለመጠበቅ የሚያግዘውን የOHR "ለአረጋውያን የሚደረግ እንክብካቤ" (Care for Seniors) ፕሮግራም አጉልተን አቅርበናል። ይህ ፕሮግራም በዲሲ ውስጥ በሚገኙ የረጅም ጊዜ እንክብካቤ መስጫ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሁሉም ሰራተኞች እና ኮንትራክተሮች በOHR እውቅና በተሰጠው አሰልጣኝ አማካኝነት ስልጠና እንደሚያገኙ ያረጋግጣል፤ እንዲሁም ነዋሪዎች በመረጡት ስም፣ ተገቢ በሆነ የግለሰብ መጠሪያ እና ከጾታ ማንነታቸው ወይም መገለጫቸው ጋር በሚስማማ መልኩ በተመደበላቸው ክፍል የመኖር መብታቸውን ያስከብራል። 

እንዲሁም ባለሙያዎች እና የዘርፉ ተሟጋቾች በየጊዜው በሚለዋወጠው የአሁኑ የስራ ዘርፍ ሁኔታ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ያካፈሉበትን የEmployment First Summit ለማዘጋጀት ከአካል ጉዳተኞች መብት ቢሮ ጋር በጋራ ሰርተናል። በዚህ ተሳትፎአችን አማካኝነት ስለሥራ ቦታ ጥበቃዎች መረጃን ማካፈል እና በሥራ ዓለም ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ጋር በቀጥታ መገናኘት ችለናል። እንዲሁም፣ የአካል ጉዳተኞች ለሥራ ዕድሎች እኩል ተደራሽነት እንዲኖራቸው እና በዲስትሪክቱ ሕግ መሠረት ያላቸውን መብቶች እንዲረዱ የማድረግን አስፈላጊነት አጠናክሮታል። 

ኦክቶበር 15  OHR በ ፐርፕል ተርስዴይ (Purple Thursday) ላይ ተሳትፏል፤ ይህ በየዓመቱ የሚካሄድ ብሔራዊ የተግባር ቀን ሲሆን፣ ዓላማውም ከቤተሰብ ውስጥ ጥቃት የተረፉትን ለመደገፍ እና ህይወታቸውን ላጡት ክብር ለመስጠት ነው። እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው ከሆነ፣ እባክዎ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ አስቸኳይ እርዳታ የሚሰጠውን 'DC Safe' የተባለውን ድርጅት፣ በቀን ለ24 ሰዓት እና በሳምንት ለ7 ቀናት በሚሰራው የ'DC Victim Hotline' ስልክ ቁጥር 844-443-5732 በመደወል ወይም dcsafe.orgደረገጽን በመጎብኘት ያግኙ። ወደፊት ስንመለከት በዚህ ወር ጋዜጣ ላይ የተጋሩትን መረጃዎችና ግብዓቶች እንድትመለከቱ አበረታታችኋለሁ። መብቶቻችንን መረዳት እና ድጋፍ የት ማግኘት እንደሚቻል ማወቅ ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን ወይም በማህበረሰባችን ውስጥ ለሚገኝ ማንኛውም ሰው ትርጉም ያለው ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። መረጃ በመለዋወጥ፣ እርስ በርስ በመተሳሰብ እና በንቃት በመሳተፍ ሁሉም ሰው ያለ አድልዎ የመኖር፣ የመሥራት፣ የመማር እና የማደግ እድል የሚያገኝበትን አካባቢ መገንባታችንን ማስቀጠል እንችላለን።